በወራቤ ከተማ ❝ከሰንበት እስከ ሰንበት❞ የገበያ ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀመረ!
በወራቤ ከተማ አስተዳደር 02 ቀበሌ ዱና የስልጤ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ፊትለፊት ❝ከሰንበት እስከ ሰንበት❞ የገበያ ማዕከል ተቋቁሞ በዛሬው ዕለት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።


በስፍራው ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር በየጊዜው ዋጋቸው እየናረ የሚገኙ የግብርና እና የፍጆታ ምርቶችን ዋጋ ለማረጋጋት በቅርቡ አምራቹን እና ሸማቹን ማህበረሰብ በቀጥታ የሚያገናኝ የግብይት ስርዓት መጀመሩ የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።


ዋና አስተዳዳሪው አክለውም የመንገድ መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት መንግሥትና ማህበረሰቡን በማስተባበርና በማቀናጀት አዳዲስ የመንገድ ከፈታና ጥገና በማድረግ አርሶአደሮች ያመረቱትን ምርት በቀላሉ ወደ ገበያ እንዲያስገቡ ለማስቻል በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የስልጤ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሸምሴ ኑሪ በበኩላቸው ከሰንበት እስከ ሰንበት የተለያዩ ምርት መሸጫ ማዕከል ሸማችን ከአምራች ጋር በቀጥታ በማገናኝት የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት በዘላቂነት በማረጋጋት ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።

የኑሮ ውድነት ለመረጋጋት መንግስት በርካታ ሥራዎችን እየሰራ ነው ያሉት አቶ ሸምሴ ኑሪ የኑሮ ውድነት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገኙበትን የገበያ ማዕከል መቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሁሉም ምርቶች ላይ እየጨመረ የመጣውን የገበያ ዋጋና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በዞን ደረጃ ያሉ የገበያ ትስስሮችን በማጠናከር ለነጋዴው እና ለሸማቹ ማህበረሰብ ምቹ ሁኔታን መፍጠር መሆኑን የወራቤ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አክመል አብደላ ገልጸዋል።


በሁሉም የገበያ ማዕከሎች የሚገኙ ነጋዴዎች የመሸጫ ዋጋ ዝርዝር ማስቀመጥ እንዳለባቸው ያሳሰቡት አቶ አክመል አብደላ አለግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን በቅድሚያ በማስተማር እንዲሁም ከአላስፈላጊ ከድርጊታቸው በማይቆጠቡ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ የእርምት እርምጀ የሚወሰድ መሆኑን ጠቁመዋል።
