የፍትህ ዘርፍ የሶስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ የምክክር መድረክ ተካሄደ!
የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት የፍትህ ዘርፍ የሶስት አመት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የውይይት መድረኩን የመሩት የወራቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ያሲን ከሊል እንደገለጹት የፍትህ ስርዓትን በማሻሻል የሚስተዋሉ ክፍተቶችና ጉድለቶች በማስተካከል በአዲስ የለውጥ ሂደት መምራት እና ያሉ ጥንካሬዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡
የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል የዘርፉ አካላት የፍትህ መዘግየትን በማስወገድ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልገሎት አሰጣጥ ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዱ አሰራሮችን ማመቻቸት እንደሚኖርባቸውም ከንቲባው አመልክተዋል።
የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አክመል ጀማል በንግግራቸው ወንጀልን መከላከል ለጸጥታ አካላት ብቻ የሚተው ሥራ አለመሆኑን ጠቅሰው የማህበረሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የወንጀልን አስከፊነት በመረዳት ሁሉም የሚመለከተው አካል አጋዥ መሆን ይገባል ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ም/ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ ወ/ሮ ሙስሊያ መሀመድ በበኩላቸው የጸጥታ አካላት መረጃ በማሰባሰብ እና በማደራጀት ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎችን በማስቀረትና ወንጀሎቹ ከመፈፀማቸው በፊት በህጋዊ መንገድ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ አንስተዋል።

በከተማዋ የፀጥታ አስከባሪ ቁጥርን በመጨመርና ሙያዊ ብቃት ያለው ፖሊስ በመገንባት ሰላምን፣ ደህንነትን እና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋልም ተብሏል።
