ስራዉ በተለያዩ ምክንያቶች ተስተጓጉሎ የነበረዉ የወራቤ ከተማ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሳራ መሆኑ ተገለጸ!
በዓለም ባንክ ብድርና ማቺንግ ፈንድ የሚገነባው የወራቤ ከተማ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።


ከዚህ ቀደም ሌሎች አስፈላጊ ቱቦዎች መግባታቸዉ የሚታወቅ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ለዚህ ፕሮጀክት አገልግሎት የሚዊሉ የተለያየ መጠን ያላቸው የኤችዲፒ ቱቦዎችና መገጣጠሚያዎች ወደ ከተማዉ በመግባት ላይ ይገኛሉ።

የማዕከላዊ እትዮጵያ ክልል የዉሃ ቢሮ የኮንትራት ስራዎች ተቆጣጣሪ የሆኑት አቶ ያሲን አማን የፕሮጀክቱ ስራዉ በተለያዩ ምክንያቶች ተጓቶ እንደነበረ በመግለጽ ክልሉ ባስቀመጠዉ አቅጣጫ መሰረት በሂደቱም ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት ግንባታዉን በአዲስ መልክ በማስጀመር በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነዉ ብለዋል።

የክልሉንና የፌደራል የውኃ ሴክተር ባለድርሻዎችን ቁርጠኝነት በማድነቅ ሃሳባቸውን የሰጡን የስልጤ ዞን ዉሃ ማዕዲንና እነርጂ መምሪያ ዋና ኃላፊ አቶ ጨፋ ከድር ለፕሮጀክቱ መሳካት ከሀገር ውጭ ተመርተው የሚገቡ ቧንቧዎች ሳንካ ሆነው እንደቆዩና አሁን ላይ ይሄ ችግር መፈታቱ የፕሮጀክቱን ገቢራዊነት ከፍ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል።

በቦታዉ የተገኙት የከተማ አስተዳደሩ ዋና የመንግሥት ተጠሪ አቶ ናስር ቡሽር ለፕሮጀክቱ የሚሆኑ ማቴሪያሎች በመግባት ላይ እንደሚገኝ በመግለጽ በከተማው የሚስተዋለውን የንጹህ መጠጥ ዉሃ እጥረት ለመቅረፍ እና ፕሮጀክቱ በአጭር ግዜ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ የበኩሉን እደሚወጣም ተናግረዋል።
የወራቤ ከተማ አስተዳደር ዉሃ አገልግሎት ባለሙያና የፕሮጀክቱ ሱፐርፋይዘር የሆኑት አቶ አብዱልፈታ ረሺድ ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ በማጠናቀቅ የከተማዉን የዉሃ ተደራሽነት ለማስፋት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የድጋፍና ክትትል ስራ ይሰራል ብለዋል።



