በዚህ በጀት ዓመት የሚጠናቀቅና 165 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት በዛሬው እለት በይፋ መጀመሩን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፍቃዱ ገለጹ!
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩና የስልጤ ዞን ዋና አስተዳደሪ፣ የዞኑ ብልፅግና ፓርቲ ዋና ኃላፊና የወራቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የወራቤ ከተማ ኮሪደር ልማትን በይፋ አስጀምረዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በዚህ በጀት ዓመት የሚጠናቀቅና 165 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ልዩ ልዩ የኮሪደር ልማት ልማት በሰባቱ የክልል ማዕከል ከተሞች በዛሬው እለት መጀመሩን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ ገልጸዋል።
አቶ አንተነህ የወራቤ ከተማ ኮሪደር ልማትን በይፋ ያስጀመሩ ሲሆን በሁሉም የክልል ማዕከል ከተሞች በይፋ መጀመሩን አስታውቀዋል።


ይህ ሁለገብ የከተሞች ልማት በሁለት ምዕራፍ የሚካሄድና 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን 2 ቢሊየን ብር በሚጠጋ በጀት በከተማው ማህበረሰብ እና መንግስት እንደሚሰራ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።


የኮሪደር ልማቱ ሳቢና ለነዋሪው ኑሮ ምቹ የሆኑ ከተሞችን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን የገለጹት አቶ አንተነህ ለልማቱ ስኬት የህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።


በሰባቱ ከተሞች የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይተው በዛሬው እለት በይፋ ስራው መጀመሩን አስረድተዋል። ከእነዚህ ከተሞች መሃል ወራቤ አንዷ መሆኗን የገለጹ ሲሆን የከተማዋን ነዋሪ በንቃት ባሳተፈ መልኩ ቀን ማታ ሳይባል ዛሬውኑ እንዲጀመርም አሳስበዋል።


የኮሪደር ልማት የስራ ባህልን በመቀየር ረገድ ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ከወዲሁ ይህን አጋጣሚ ለለውጥ እንዲጠቀምበትም ጥሪ አቅርበዋል።
የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ በበኩላቸው ምቹ የሆነውን ፕላን በመጠቀም የወራቤ ከተማን ዘመናዊና ተወዳዳሪ ለማድረግ በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል። በተለይም ደግሞ ከተማዋን ማራኪ ከማድረግ ባሻገር የኢንቨስትመንትና ኢንደስትሪ ማዕከል ለማድረግ ጅምር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ዋና አስተዳዳሪው አረጋግጠዋል።

ለዚህ ስኬት የከተማዋም ሆነ የዞኑ ማህበረሰብ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። በወራቤ ከተማ በዛሬው እለት በይፋ የተጀመረው ይህ ልማት ደረጃውን የጠበቀ አደባባይ፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የመዝናኛ ማዕከላት፣ የወንዝ ዳርቻዎች ልማትና ሌሎችንም እንደሚያካትት አስታውቀዋል።
የወራቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ያሲን ከሊል እንዳሉት ደግሞ ለኮሪደር ልማቱ ስኬት ባለፉት ሶስት ወራት የዲዛይን ዝግጅትን ጨምሮ ልዩ ልዩ ቅድመ ዝግጅቶች ተደርገዋል።

በከተማ ደረጃ 25 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ልማት ይሰራል ያሉት ከንቲባው በመጀመሪያው ምዕራፍ 8 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የእግረኛና ተሽከርካሪ መንገዶች፣ 5 ሄክታር ፓርክ፣ አረንጓዴ መናፋሻዎች፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና ሌሎችም ልማቶች ይካሄዳሉ።
ለዚህ ልማት በትናንትናው እለት የልማት አካባቢውን የማጽዳት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በኮሪደር ልማት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የክልሉ፣ የስልጤ ዞንና ወራቤ ከተማ አስተዳደር አመራሮችና የወራቤ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።