የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ውጤታማ የልማት ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል – የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ!
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ይህን ያሉት በስልጤ ዞን ልዩ ልዩ የልማት ስራዎችን በጎበኙበት ወቅት።
ታህሣሥ 3/2017 [ወራቤ ኮሙኒኬሽን] በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የተመራው ልዑክ በዛሬው ዕለት በስልጤ ዞን በነበራቸው ቆይታ በአልቾውሪሮ፣ ስልጢ፣ ምስራቅ ስልጢ ወረዳዎች እየተከናወኑ ያሉ የግብርና ልማት ስራዎች፣ የወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እንዲሁም በወራቤ ከተማ ሶጃት የኢንዱስትሪ መንንደር የስራ እንቅስቃሴ ተዟዙረው ጎብኝተዋል።


በዚሁ ወቅት ያነጋገርናቸው የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በስልጤ ዞን በነበራቸው ቆይታ የተመለከቷቸው የልማት ስራዎች የሚበረታቱ እና እንደ ሀገር ተሞክሮ ሊወሰድባቸው የሚችሉ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም በየደረጃው እየተከናወኑ ያሉ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች በቀጣይ ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አንስተዋል።
የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት የህብረተሰቡን ህይወት በተጨባጭ ለመቀየር በሁሉም ዘርፎች ርብርብ ሲደረግ መቆየቱን አስረድተዋል።


በዚህም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ውጤት ታይቶበታል ብለዋል።
በአልቾ ውሪሮ በኩታ ገጠም የለማ የስንዴ ማሳ እና በሌማት ትሩፋት ገቢያቸውን እያሻሻሉ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
በወረዳው በቀጨሞ ቀበሌ 37 አርሶ አደሮች ኩታ ገጠም ተደራጅተው በ15 ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን የስንዴ ሰብል ጎብኝተዋል።
መሬቱ ከዚህ ቀደም በአሲድ የተጠቃ መሬትን በኖራ በማከም ምርታማነት በማሳደግ ለስንዴ ዘር ብዜት የሚሆን ምርት የሚለማበት ስለመሆኑም ተገልጿል።
በ2016/2017 የመኸር ወቅት በስልጤ ዞን 27 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በኩታ ገጠም መልማቱ ተመልክቷል።


ልዑኩ በስልጢ ወረዳ በመናኸሪያ 01 ቀበሌ ሌማት የዶሮ እርባታና ሀይረንዚ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማህበራትን ሚኒስትሩ ጎብኝተዋል።
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው በዶሮ እርባታ እና በእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ዘርፍ የተደራጁ ወጣቶች ከተቀጣሪነት ወጥተው ለሌሎች ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻላቸው ተጠቁሟል።
የማህበራቱ የገቢ አቅም ከ23 ሚሊየን በላይ ብር የደረሰ ሲሆን የአካባቢውን ገበያ በማረጋጋት ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት መቻላቸውም ተመላክቷል።
ሚኒስትሩ በዞኑ ምስራቅ ስልጢ ወረዳ በነበራቸው ቆይታ በ45 ሄ/ር መሬት ላይ 831 አርሶ አደሮች የተሳተፉበትን የሙዝ እርሻ ምልከታ አድርገዋል።
የአካባቢው አርሶ አደሮች የመሬታቸውን ምርታማነት ይቀንስ የነበረውን ባህር ዛፍ በመንቀል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለውን ሙዝ በሰፊው ማልማት መቻላቸው በመስክ ምልከታው በአብነት ተጠቅሷል።

የስልጤ ሀይቅ በመስኖ በመጥለፍ እየለማ ባለው የሙዝ እርሻ የአካባቢው አርሶ አደሮች የኢኮኖሚ አቅማቸውን ከማሳደግ ባለፈ በስራ ባህላቸው ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ስለመቻላቸው ተገልጿል።
ሚኒስትሩ እና በእርሳቸው የተመራው ልኡክ በሰዳ ጎራ ቀበሌ በ10 ሄ/ር መሬት ላይ እየለማ ያለ የአቮካዶ ክላስተር ምልከታ አድርገዋል።
32 ወጣቶች የተሳተፉበት የአቮካዶ ክላስተር በአካባቢው ለሚገኙ አርሶ አደሮች የተሞክሮ ማዕከል መሆን ስለመቻሉም ተመላክቷል።
በመጨረሻም ሚኒስትሩ የህብረተሰብ ተሳትፎ የጎላበት የልማት ስራ ውጤታማ መሆኑ አንዱ ማሳያ የሆነውን የወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና በወራቤ ከተማ ሶጃት የኢንዱስትሪ መንደር የስራ እንቅስቃሴ ምልከታ በማድረግ ጉብኝታቸውን አጠቃለዋል።(ስዞመኮ)

