የወራቤ ከተማ አስተዳደር ለከተማው የህብረተሰብ ክፍሎች የምስጋና መልዕክት አስተላለፈ!
❝መላው የወራቤ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች፡ በከተማችን የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ለማስጀመር ከዲዛይን ጀምሮ በርካታ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።
ታዲያ የኮሪደር ልማት ስራውን ተግባራዊ ለማድረግ ከቅድመ ዝግጅቱ ጀምሮ ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ ላበረከቱ እና ለልማቱ ቅድሚያ በመስጠት ቁርጠኛነታቸውን ላሳዩ ለመላው የከተማው ነዋሪዎች፣ አመራሮች፣ ነጋዴዎች፣ ባለሀብቶች፣ የፀጥታ አካላት፣ ለወጣቶችና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት በከተማ አስተዳደሩ ስም ላቅ ያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀሳብ አመንጪነት በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውንና በተግባር ላይ ያለውን የኮሪደር ልማት እንደ ከተማችን ወደተግባር ለማስገባት ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቆ እነሆ ነገ እሁድ ታህሳስ 6 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ይጀመራል።
በዚህ የማብሰሪያ መርሃ-ግብር ላይም የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዞን አመራሮችና ባለድርሻ አካላት፣ የከተማ አስተዳደሩ የአመራር አካላትና የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ባለድርሻዎች ይሳተፋሉ።
ምቹና ማራኪ የመኖሪያ አካባቢዎችን ለመፍጠር እና ዘላቂ ልማትን ለማስፋፋት ዓላማ ያደረገውን የኮሪደር ልማት ስራ በነገው ዕለት በይፋ ለማስጀመር በሚካሄደው ፕሮግራም ላይ ሁሉም የከተማዋ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ወጣቶችና የሚመለከታቸው አካላት ጠዋት 2 ሰዓት ተኩል ሪያድ ሆቴል ፊትለፊት እንድትገኙ በአክብሮት መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።
መላው የከተማችን ነዋሪዎች፡ እንደወትሮው ሁሉ በቀጣይም ለከተማችን ሁለንተናዊ ዕድገትና ለውጥ በጋራ ተግተን እንሰራለን።❞
የወራቤ ከተማ አስተዳደር
ታህሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም – ወራቤ