የከተማው ጤና ጣቢያ የህዝብ ፎረም መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሄደ!
መጋቢት 25/2017 [ወራቤ ኮሙኒኬሽን] የወራቤ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት የ2017 ዓ.ም የሶስተኛ ሩብ ዓመት የህዝብ ፎረም መድረክ አካሂዷል።
የዕለቱን መድረክ የመሩት የወራቤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነስሬ አማን ሁሉን-አቀፍ የጤና ሽፋን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አቶ ነስሬ አማን አክለውም የከተማዋን የህብረተሰብ ክፍሎችን ከበሽታ መታደግ፤ የጤና አገልግሎትን በፍትሃዊነት ማግኘት እንዲችሉ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን ከፍ ማድረግ እንደሚገባም አብራርተዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታጁዲን ሁሴን በበኩላቸው ህብረተሰቡ የግልና የአካባቢውን ንፅህና መጠበቅና የህዝብ መፀዳጃ ቤቶችን መገንባት እንዳለበት ገልፀው የደረቅና የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን ጠብቆ በማስወገድ ተላላፊ በሽታዎችን መከላከል እንደሚቻል አንስተዋል።
በሌላበኩል የኤች.አይ.ቪ ኤድስ በሽታ ጉዳይ እየተረሳና ትኩረት እያጣ መሆኑን ያነሱት አቶ ታጁዲን ሁሴን የበሽታውን ስርጭት ይበልጥ ለመግታት በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የጤና ባለሙያዎችን ዕውቀትና ክህሎት በማሻሻል በጤና ስነ-ምግባሩ መሰረት ስራቸውን እንዲያከናውኑ በማድረግ ማህበረሰቡ የሚፈልገውን አገልግሎት በቅንነት መስጠት እንዳለባቸው በመድረኩ ተጠቁሟል።
የእናቶችና ህፃናት ሞት እንዲሁም ተላላፊ በሽታዎች እየቀነሱ እንዲመጡና የህብረተሰቡ ጤና በተሻለ መልኩ ለመጠበቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተነስቷል።