የጤና መድህን ህዝቡን ለህክምና ቋሚ ንብረቱን ከመሸጥ ታድጎታል – የወራቤ ከተማ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታጁዲን ሁሴን!
መጋቢት 27/2017 [ወራቤ ኮሙኒኬሽን] የጤና መድህን፣ ህዝቡን ለህክምና ቋሚ ንብረቱን ከመሸጥ ታድጎታል ሲሉ የወራቤ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታጁዲን ሁሴን ገለጹ።
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተግባራዊ መደረጉ የከተማችንን ህዝብ ወደ ህክምና የመሄድ ልምድ በመጨመር፣ የህክምና ተቋማቱንም፣ ታካሚዎችን የማስተናገድና የፋይናንስ አቅማቸው እንዲሻሻል አድርጓል ያሉት አቶ ታጁዲን፣ ተቋማቱ የነበረባቸውን የመድሃኒት አቅርቦትና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር በዚህ አመት መቅረፋቸውንም ተናግረዋል።
የመክፈል አቅምን መሰረት ያደረገውን የመዋጮ አሰባሰብ ስርዓት ተግባራዊ በመደረጉ፣ ከአባላት የሚሰበሰብውን ገንዘብ በጅጉ ከማሳደጉም ባሻገር ዝቅትተኛ ገቢ ያላቸውን ከፋይ አባላትን አቅም ያገናዝበ የገንዘብ መጠን እንደከፍሉ አስችሏል ሲሉ የነገሩን ኃላፊው፣ በያዘነው አመት በአጠቃላይ ከአባላትና ከድጎማ ከ15 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን ኃላፊው ገልጸዋል።
በወራቤ ከተማ አስተዳደር 10ሺህ 770 የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አባላት ያሉ ሲሆን 2 ሺህ ያህሉ፣ መክፈል የማይችሉ መሆናቸው ተመላክቷል።
አቶ ታጁዲን ሁሴን ለኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት እንደገለጹት የከተማ አስተዳደሩ 2 ሚሊየን 630 ሺህ ብር በመደጎም ለጤና መድህን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የህዝብ ጉዳይ በመሆኑ በየደረጃው ያሉ የፖለቲካ አመራሮች ለዘርፉ ተግባራዊነት ያሳዩት ቁርጠኝነት የስኬቶቻችን ሚስጥሮች ናቸው ያሉን ኃላፊው ህዝባችን ያለምንም የጤና ወጭ ስጋት ከጤና ጣቢያ እስከ ሆስፒታል ሃብት ንብረቱን ሳይሸጥ እየታከመ በመሆኑ አጠናክረን እንሰራለን ብለዋል።
አንዳንድ ሆስፒታሎች የተጋነነ የአገልግሎት ከፍያ ይጠይቃሉ፤ ይህም የጤና መድህኑን ፋይናንስ አቅምና የአገልግሎት ጥራቱን ይጎዳል ያሉት ሃላፊው የኦዲት ስርዓቱን በማጠናከር፣ የመረጃ አያያዝ ዘዴ በማዘምን፣ ከመታወቂያ ጋር የሚከሰቱ ችግሮችን በመፍታት፣ እንዲሁም በየደረጃው የሰው ሀብቱን በማሟላት ከዚህ የተሻለ ስራ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።