ጉዟችን ረጅም እና ጅምራችን አስተማማኝ እንዲሆን ሁሉንም መንግስታዊ አገልግሎት በእውቀት መምራት ያስፈልጋል – ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው!
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትብብር በፐብሊክ ኢንተርፕሪነርሺፕ እና የኢኖቬሽን ሥነ ምህዳርን ምቹ ለማድረግ ያለመ ስልጠና ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች በቢሾፍቱ ከተማ መሰጠት ጀምሯል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከ600 ሚሊየን በላይ ችግኞችን በአንድ ጀንበር በመትከል ሪከርድ የሰበረችበት እና ለአለም ህዝብ ተምሳሌት የሆነችበት ወቅት ላይ በመሆናችን ስልጠናውን የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በእያንዳንዱ የዓለም ህዝብ ቁጥር ልክ ችግኝ እየተከለች ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህም ለዘርፉ መንግስት ልዩ ትኩረት በመስጠቱ የተገኘው ውጤት አበረታች ነው ብለዋል።
ጉዟችን ረጅም እና ጅምራችን አስተማማኝ እንዲሆን ሁሉንም መንግስታዊ አገልግሎት በእውቀት መምራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በተለያየ ደረጃ የተገኘውን እውቀት እና ክህሎት ለስራ እድል ፈጠራ፣ዘላቂ ገቢ የሚያስገኝ እና ንግድን የሚያሳካ ሊሆን እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው ጠቁመዋል።

በንባብ ያዳበርናቸውን፣የሰማናቸውን እና ያየናቸውን ጉዳዮች በእውቀት እና በክህሎት በመተርጎም ለችግሮቻችን መፍቻ እንዲውሉ በማድረግ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት ተገቢ ስለመሆኑም ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል እንደገለጹት በሀገሪቱ ከስራ እድል ፈጠራ ባሻገር የሲቪል ሰርቪሱን የስርዓት ሂደት መቀየር የሚያስችል የሪፎርም ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎች እንዲበረታቱ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ያጋጠሙ ችግሮችን ወደ እድል በመቀየር መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ተቋማት በፈጠራ መነጽር ችግሮችን አሻግሮ በመመልከት የመፍትሄ ሀሳብ ማፍለቅ እንደሚገባ የተናገሩት ሚኒስትሯ ትልቁ ሀገራዊ አጀንዳችን የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እይታ ላይ ያተኩራል ብለዋል።
የራሳችንን መንገድ ፈልጎ ማግነት ይገባል ያሉት ሚኒስትሯ ከአይቻልም መንፈስ ወጥተን ስራችንን በይቻላል እሳቤ ማከናወን ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል።
ሰላማዊ፣በዴሞክራሲ የበለጸገች፣እንዲሁም እድገቷ ሙሉ የሆነች ሀገር ለመገንባት ትክክለኛውን መንገድ እና አካሄድ መከተል እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የአመራር ስልጠናው ለተከታታይ ሶስት ቀናት እንደሚቆይ ተመላክቷል።መረጃው የክልሉ ኮሙኒኬሽን ነው።
