ትውልዱ የጀመረው የባህር በር የማግኘት የሕልውና ጥያቄ ምላሽ እስከሚያገኝ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት – ምሁራን
ትውልዱ የጀመረውን የባህር በር የማግኘት የሕልውና ጥያቄ ምላሽ እስከሚያገኝ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ምሁራን አስገነዘቡ።
በአፍሪካ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት እና የፈጣን ኢኮኖሚ ዘዋሪ የሆነችው ኢትዮጵያ ሕልውናዋ የወደቀው በጅቡቲ ኮሪደር ላይ ነው።
ኢትዮጵያ በአህጉሩ ከሚገኙ 16 የባህር በር ከሌላቸው ሀገራት አብላጫ የሕዝብ ቁጥር በማስመዝገብ ቀዳሚውን ስፍራ ትይዛለች።
ከቀይ ባህር 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሀገሪቱ በአንድ የባህር በር አማራጭ 95 በመቶ የሚሆነው የገቢ እና የወጪ ንግዷ በጅቡቲ ጠባብ ኮሪደር የሚመላለስ ነው።
ይህም ለውጥ እና የኢኮኖሚ ሪፎርም እያደረገች ለምትገኝ ሀገር ትልቅ መሰናክል ከመሆኑ ባሻገር የጅቡቲ ወቅታዊ ሁኔታ ኢትዮጵያንም የሚዘውር እየሆነ መጥቷል።
ለዚህም ባሳለፍነው ሳምንት የኢድ-አልፊጥርን በዓል አስመልክቶ በጅቡቲ ለተከታታይ ቀናት ሥራ መዘጋቱ ያስከተለው የነዳጅ እጥረት ከብዙ በጥቂቱ ለአብነት ተጠቃሽ ነው።
የሰላም ተመራማሪ እና መምህር የሆኑት ዶ/ር ገለታ ሲሜሶ፣ የራሱን ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ውሳኔ በሚሰጥ አንድ ሀገር ላይ የተመረኮዘ የባህር በር አማራጭ ከፍ ያለ ዋጋ እንደሚያስከፍል ያስረዳሉ።
እያንዳንዱ የግዢ እና ሽያጭ ሸቀጦቿ የአደባባይ ምሥጢር የሆኑባት ኢትዮጵያ ለሀገር ሕልውና ወሳኝ የሆነው የጦር መሣሪያ፣ ትላልቅ ማሽነሪዎች፣ ሸቀጣ ሸቀጥ እና ሌላ መሰል ነገሮችን የማስገባት እና ማስወጣት እንቅስቃሴዋ በአንድ ሀገር የፍቃድ እጅ ላይ የወደቀ መሆኑን ያነሣሉ።
ይህም የሀገሪቱን የዕድገት፣ የደኅንነት፣ የቀጠናውን ተሳትፎ፣ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ግንኙነት የሚወስን መሆኑን ነው ለኢቢሲ ዶትስትሪም የገለጹት።
ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ ዕቃዎች ማጓጓዣ ወጪ የሸቀጡን 27 በመቶ የሚይዝ ሲሆን ነገሮች በዚሁ ከቀጠሉ ጅቡቲ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ እንደምትሆን ጠቁመዋል።
በጅቡቲ ያለመረጋጋት፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ የዲፕሎማሲ መሻከር እንዲሁም የተሻለ ጥቅም ከሚሰጥ አካል ጋር ስምምነት ብታደርግ ኢትዮጵያ በአማራጭነት ልትጠቀመው የምትችል የባህር በር የላትም ሲሉ ያለውን ስጋት ዘርዝረዋል።
ለዚህም ትውልዱ የጀመረው የባህር በር የማግኘት የሕልውና ጥያቄ ምላሽ እስከሚያገኝ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ይላሉ።
የሀገር ውስጥ ሰላም ማስፈን፣ ዕድገትን ማፋጠን እና ዴሞክራሲን ማስረፅ አንድ ሀገር ለምታነሣው የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንድታገኝ የሚያስችላት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን የዓባይ ጂኦ ፖለቲካ ተንታኝ እና ተደራዳሪ የሆኑት አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ይናገራሉ።
የተጠቀሱትን ነጥቦች ካሳካች ሀገር ጋር መስተጋብር መፍጠር የማይፈልግ ሀገር የለም ያሉት አቶ ፈቅአህመድ፣ አማራጮቹን ከሚሰጡ ሀገራት ጋር ያለ ግንኙነትን ማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑንም ያነሳሉ።
አያይዘው የኢትዮጵያ የወደብ ተጠቃሚነት በዓለም አቀፍ ሕግ የሚደገፍ በመሆኑ የሀገርን ሁኔታ በማጠናከር የመብቱ ተጠቃሚ ልንሆን እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
ምንጭ፦ ኢቢሲ