
Uncategorized

❝መላው የወራቤ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች፡ በከተማችን የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ለማስጀመር ከዲዛይን ጀምሮ በርካታ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።
ታዲያ የኮሪደር ልማት ስራውን ተግባራዊ ለማድረግ ከቅድመ ዝግጅቱ ጀምሮ ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ ላበረከቱ እና ለልማቱ ቅድሚያ በመስጠት ቁርጠኛነታቸውን ላሳዩ ለመላው የከተማው ነዋሪዎች፣ አመራሮች፣ ነጋዴዎች፣ ባለሀብቶች፣ የፀጥታ አካላት፣ ለወጣቶችና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት በከተማ አስተዳደሩ ስም ላቅ ያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀሳብ አመንጪነት በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውንና በተግባር ላይ ያለውን የኮሪደር ልማት እንደ ከተማችን ወደተግባር ለማስገባት ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቆ እነሆ ነገ እሁድ ታህሳስ 6 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ይጀመራል።
በዚህ የማብሰሪያ መርሃ-ግብር ላይም የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዞን አመራሮችና ባለድርሻ አካላት፣ የከተማ አስተዳደሩ የአመራር አካላትና የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ባለድርሻዎች ይሳተፋሉ።
ምቹና ማራኪ የመኖሪያ አካባቢዎችን ለመፍጠር እና ዘላቂ ልማትን ለማስፋፋት ዓላማ ያደረገውን የኮሪደር ልማት ስራ በነገው ዕለት በይፋ ለማስጀመር በሚካሄደው ፕሮግራም ላይ ሁሉም የከተማዋ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ወጣቶችና የሚመለከታቸው አካላት ጠዋት 2 ሰዓት ተኩል ሪያድ ሆቴል ፊትለፊት እንድትገኙ በአክብሮት መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።
መላው የከተማችን ነዋሪዎች፡ እንደወትሮው ሁሉ በቀጣይም ለከተማችን ሁለንተናዊ ዕድገትና ለውጥ በጋራ ተግተን እንሰራለን።❞
የወራቤ ከተማ አስተዳደር
ታህሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም – ወራቤ

#የኮሪደር_ልማት_ቅደመ_ዝግጅት_በወራቤ!
በወራቤ ከተማ አስተዳደር የኮሪደር ልማት ቅድመ-ዝግጅት በተጠናከረ መንገድ እየተሰራ ነው።
ታህሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም
ጉዟችን ረጅም እና ጅምራችን አስተማማኝ እንዲሆን ሁሉንም መንግስታዊ አገልግሎት በእውቀት መምራት ያስፈልጋል – ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው!
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትብብር በፐብሊክ ኢንተርፕሪነርሺፕ እና የኢኖቬሽን ሥነ ምህዳርን ምቹ ለማድረግ ያለመ ስልጠና ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች በቢሾፍቱ ከተማ መሰጠት ጀምሯል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከ600 ሚሊየን በላይ ችግኞችን በአንድ ጀንበር በመትከል ሪከርድ የሰበረችበት እና ለአለም ህዝብ ተምሳሌት የሆነችበት ወቅት ላይ በመሆናችን ስልጠናውን የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በእያንዳንዱ የዓለም ህዝብ ቁጥር ልክ ችግኝ እየተከለች ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህም ለዘርፉ መንግስት ልዩ ትኩረት በመስጠቱ የተገኘው ውጤት አበረታች ነው ብለዋል።
ጉዟችን ረጅም እና ጅምራችን አስተማማኝ እንዲሆን ሁሉንም መንግስታዊ አገልግሎት በእውቀት መምራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በተለያየ ደረጃ የተገኘውን እውቀት እና ክህሎት ለስራ እድል ፈጠራ፣ዘላቂ ገቢ የሚያስገኝ እና ንግድን የሚያሳካ ሊሆን እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው ጠቁመዋል።
በንባብ ያዳበርናቸውን፣የሰማናቸውን እና ያየናቸውን ጉዳዮች በእውቀት እና በክህሎት በመተርጎም ለችግሮቻችን መፍቻ እንዲውሉ በማድረግ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት ተገቢ ስለመሆኑም ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል እንደገለጹት በሀገሪቱ ከስራ እድል ፈጠራ ባሻገር የሲቪል ሰርቪሱን የስርዓት ሂደት መቀየር የሚያስችል የሪፎርም ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎች እንዲበረታቱ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ያጋጠሙ ችግሮችን ወደ እድል በመቀየር መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ተቋማት በፈጠራ መነጽር ችግሮችን አሻግሮ በመመልከት የመፍትሄ ሀሳብ ማፍለቅ እንደሚገባ የተናገሩት ሚኒስትሯ ትልቁ ሀገራዊ አጀንዳችን የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እይታ ላይ ያተኩራል ብለዋል።
የራሳችንን መንገድ ፈልጎ ማግነት ይገባል ያሉት ሚኒስትሯ ከአይቻልም መንፈስ ወጥተን ስራችንን በይቻላል እሳቤ ማከናወን ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል።
ሰላማዊ፣በዴሞክራሲ የበለጸገች፣እንዲሁም እድገቷ ሙሉ የሆነች ሀገር ለመገንባት ትክክለኛውን መንገድ እና አካሄድ መከተል እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የአመራር ስልጠናው ለተከታታይ ሶስት ቀናት እንደሚቆይ ተመላክቷል።መረጃው የክልሉ ኮሙኒኬሽን ነው።
በስልጤ ዞን የካሊድ ዲጆ መስኖ ፕሮጀክት ግንባታን ለማስቀጠል የሚያስችል ጉብኝት ተደረገ!!
ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን የካሊድ ዲጆ መስኖ ፕሮጀክትን ከተቋረጠበት ለማስቀጠል የሚያስችል ጉብኝት ተደርጓል፡፡
በጉብኝቱ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሊ ከድር፣ እንዲሁም ሌሎች የፌዴራል ኮንስትራክሽን ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የጉብኝቱ ዓላማም ተጀምሮ የተቋረጠውን የካሊድ ዲጆ የመስኖ ፕሮጀክትን መልሶ ማስጀመርን ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል፡፡
ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ(ዶ/ር) ለጨረታ የሚያግዙ አስፈላጊ ዝግጅቶች በኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በአጭር ጊዜ ተዘጋጅተው ለጨረታ እንዲቀርቡ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስራው በወራቤ ከተማ ተጠናክሮ ቀጥሏል!
የወራቤ ከተማ አስተዳደር አመራሮች በከተማው ዳጤ-ወዚር ቀበሌ በሚገኘው ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህብ ሥፍራ በ”ጉድሮ” ደን ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ልማት የችግኝ ተከላ ሥራው ላይ የወራቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ያሲን ከሊልን ጨምሮ የከተማው አስተባባሪዎች፣ አመራሮችና የቀበሌው ነዋሪዎች የተሳተፉ ሲሆን የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞችን እና አገር በቀል የጥላ ዛፎችን ተክለዋል።
በዚሁ ወቅት መልዕክት ያስተላለፉ አቶ ያሲን ከሊል በስፍራው የተተከሉ ችግኞች እንዲፀድቁ የአካባቢው ማህበረሰብ በእኔነት መንፈስ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መንከባከብ እና ተጨማሪ የተለያዩ ችግኞችን መትከል እንዳለበት ምክረ-ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል በዘንድሮው የክረምት ወራት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር በዳጤ-ወዚር ቀበሌ ቤት እየተገነባላቸው ለሚገኙ አቅመ-ደካሞች የተዘጋጀውን ቆርቆሮ ከተማ አስተዳደሩ አስረክቧል።
የፍትህ ዘርፍ የሶስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ የምክክር መድረክ ተካሄደ!
የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት የፍትህ ዘርፍ የሶስት አመት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የወራቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ያሲን ከሊል እንደገለጹት የፍትህ ስርዓትን በማሻሻል የሚስተዋሉ ክፍተቶችና ጉድለቶች በማስተካከል በአዲስ የለውጥ ሂደት መምራት እና ያሉ ጥንካሬዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡
የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል የዘርፉ አካላት የፍትህ መዘግየትን በማስወገድ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልገሎት አሰጣጥ ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዱ አሰራሮችን ማመቻቸት እንደሚኖርባቸውም ከንቲባው አመልክተዋል።
የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አክመል ጀማል በንግግራቸው ወንጀልን መከላከል ለጸጥታ አካላት ብቻ የሚተው ሥራ አለመሆኑን ጠቅሰው የማህበረሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የወንጀልን አስከፊነት በመረዳት ሁሉም የሚመለከተው አካል አጋዥ መሆን ይገባል ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ም/ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ ወ/ሮ ሙስሊያ መሀመድ በበኩላቸው የጸጥታ አካላት መረጃ በማሰባሰብ እና በማደራጀት ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎችን በማስቀረትና ወንጀሎቹ ከመፈፀማቸው በፊት በህጋዊ መንገድ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ አንስተዋል።
በከተማዋ የፀጥታ አስከባሪ ቁጥርን በመጨመርና ሙያዊ ብቃት ያለው ፖሊስ በመገንባት ሰላምን፣ ደህንነትን እና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋልም ተብሏል።
በገቢ አሰባሰብ እና በሂደቱ በሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዉይይት ተካሄደ!
መጋቢት 14/2016 [ወራቤ ኮሙኒኬሽን] በወራቤ ከተማ አስተዳደር በግብር አሰባሰብ እና በሂደቱም በሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር የዉይይት መድረክ ተካሂዷል።
የሊዝ ዉዝፍ ዕዳ አመላለስ፣ ከሼድና ኮንቲነር ገቢ፣ የአከራይ ተከራይ ገቢ፣ ከደረሰኝ አጠቃቀም፣ የማዕድን ዘርፍ ግብር፣ ከንግድ ፈቃድ እና በሌሎችም ግብር በሚሰበሰብባቸዉ ዘርፎች ላይ በሚስተዋሉና በሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ላይ ሰፊ ዉይይት ተደርጓል።
መድረኩን የመሩት የወራቤ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብዱልከሪም ሸሳይድ እንዳሉት ገቢ የሚሰበሰብበት በርካታ ዘርፍ መኖሩን እንዲሁም መጠቀም ያልተቻለ ሃብት ያለ መሆኑን ገልጸዉ በቀጣይ ሁሉም ባለድርሻ አካል እገዛ በማድረግ የከተማዋን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ገቢ የመሰብሰብ ተግባሩን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
በዉይይት መድረኩም በግብር አሰባሰብ እና በሂደቱም በሚስተዋሉ ማነቆዎች ዙሪያ ያተኮረ ሰነድ በከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ጽ/ቤት ሃላፊ በአቶ ከድር ሸኑሪ ቀርቦ ባላድርሻ አካላቱ በጥልቀት መክረዉበታል።
በከተማው መሳካት ያለባቸዉ የተለያዩ የልማት ስራዎችና ፕሮጀክቶች እንደ ሀገር ባጋጠሙ የኢኮኖሚ ዉስንነት እንዲሁም በአግባቡ ሀብትን መሰብሰብ ባለመቻሉ ለመቆም መገደዳቸው የተጠቆመ ሲሆን በንግድ እንቅስቃሴ ላይ ለሚፈጸም የትኛውም አይነት ግብይትና አገልግሎት ደረሰኝ በመስጠትና በመቀበል ከዘርፉ የሚገኝ ገቢን ማሳደግ ይገባል ነዉ የተባለው።
ህዝቡ የሚያነሳቸዉን የልማት ፍላጎቶችን ለማሟላት እና የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ለማስፋት ግብር ወሳኝ በመሆኑ ገቢን በሁሉም ዘርፍ አሟጦ መሰብሰብ ያስፈልጋል ሲሉ የከተማው ገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከድር ሸኑሪ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ዉዝፍ ዕዳ ያለባቸዉ በግዜ እንዲከፍሉ በማድረግ እንዲሁም ከቅጣት የሚድኑበትን አሰራር መከተል እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን አልፎ አልፎ ህግና-ደንብን ተላልፈዉ በሚገኙ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ መዉሰድና ተጠያቂነትን ማስፈን ያስፈልጋል ተብሏል።